የሙዚቃ አቀናባሪ፣ ገጣሚና የዜማ ደራሲ ኤልያስ መልካ አረፈ

አቀናባሪ ኤልያስ መልካ

የፎቶው ባለመብት, Fana Broadcasting corporate

የኤሊያስ መልካ የቀብር ሥነ ሥርዓት ሰኞ እንደሚፈፀም የሙዚቃ ባለሙያው አቶ ዳዊት ይፍሩ ለቢቢሲ ተናገሩ። የቀብር ሥነ ሥርዓቱንም ለማስፈፀም ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።

አቶ ዳዊት እንዳሉት ቀብሩ የሚፈፀመው ሰኞ 9 ሰዓት ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ሲሆን በቅድሚያ ግን አስክሬኑ ኤልያስ ሙዚቃን ወዳጠናበት የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ተወስዶ የክብር ሽንት ይደረግለታል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ባሕል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ የሆኑት ሰርፀ ፍሬ ስብኀት የሚመሩት ኮሚቴ በመንግሥት በኩል ያሉ ቀብሩን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ለማስፈፀም እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት በቀብሩ ላይ ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።

የሙዚቃ አቀናባሪ፣ ገጣሚ፣ የዜማ ደራሲ እና ጊታሪስት የሆነው ኤልያስ መልካ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ የተሰማው ዛሬ ማለዳ ነበር።

ሙዚቀኛ ኤልያስ መልካ የስኳር እና ኩላሊት ህመም ገጥሞት ህክምናውን ሲከታተል መቆየቱን የቅርብ ጓደኞቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አዲስ አበባ ውስጥ አዲስ ከተማ ተብሎ በሚጠራውና ልዩ ስሙ አብነት በሚባለው ሰፈር የተወለደው ኤልያስ መልካ በልጅነቱ ጥሩ እግር ኳስ ተጫዋች እንደነበር ወዳጆቹ ይናገራሉ።

በልጅነቱ አብረው የሰንበት ትምህርት በወንጌላውያን አማኞች ቤተ ክርስቲያን እየተማሩ ማደጋቸውን የሚናገረው ገጣሚ ዳዊት ፀጋዬ፣ ፒያኖ እና ጊታር ቤታቸው እየመጣ ይጫወት እንደነበር ያስታውሳል።

ኤልያስ መልካ በአዲስ ከተማ ገነት ወንጌላውያን አማኞች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያገለግል እንደነበር የሚናገረው ዳዊት፣ ኤሊያስ መልካ በጣም ተጫዋች፣ የዋህና ቅን እንደነበር ያስታውሳል።

አቶ ዳዊት ይፍሩ በበኩላቸው ኤሊያስን በቅርበት ያወቁት ከሦስት ዓመት ወዲህ መሆኑን ይጠቅሳሉ። ከዚያ በፊት በሥራዎቹ ብቻ ነበር የማውቀው የሚሉት አቶ ዳዊት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ "የሙዚቃ ባለሙያዎች መብት አልተከበረም፣ ሥራቸው አላግባብ እየተነገደበት ነው፣ ጥቅም አላገኙም" በሚል እንቅስቃሴን በመጀመር ሲመራ እንደነበር ይናገራሉ።

"ኤልያስ ለራሱ ሳይሆን ለሌሎች መኖር የታገለ ነበር" ሲሉም ይገልፁታል። ሥራዎቹ ዝም ተብለው የሚተዉ አይሆንም የሚሉት አቶ ዳዊት ይፍሩ፣ ተሰብስበው እንዲጠኑና በክብር እንዲቀመጡ ለእርሱም ቋሚ መታሰቢያ ለማኖር ሙዚቀኛው እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ኤሊያስ መልካ ዕድሜው በአርባዎቹ መጀመሪያ ላይ የነበረ ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ኃይሉ ተስፋዬ የሚባል ትምህርት ቤት ከዚያም ከስምንተኛ ክፍል ጀምሮ ከፍተኛ 7 ትምህርት ቤት ተምሯል።

ኤልያስ ወደ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት በ1987 ዓ.ም ገብቶ የተማረ ሲሆን በዋናነት ቼሎ አጥንቷል።

ኤሊያስ ሙዚቃን ማቀናበር የጀመረው 'በገና ስቱዲዩ'ን አቋቁሞ ሲሆን በሙያው ታታሪና ጎበዝ እንደነበር አብረውት የሰሩ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ኤልያስ መልካ በዋናነት ሊድ ጊታር ከመጫወት ባለፈ የሙዚቃና የዜማ ደራሲ እንዲሁም አቀናባሪ ነበር።

ኤሊያስ በመዲና፣ ዜማ ላስታስ እና አፍሮ ሳውንድ ባንዶች ውስጥ ተጫውቷል።

ኤሊያስ መልካ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ውስጥ እያለ በኦሮምኛ ሙዚቃ ውስጥ ያሉ የተለያዩ የድምፅና የቅኝት አደራደሮች ላይ የሰራው አነስተኛ ጥናት በዘርፉ ተጠቃሽ መሆኑን መምህራኖቹ ይናገራሉ።

በቅርቡም ከሙያ አጋሮቹ ጋር በመሆን አውታር የተሰኘ የሙዚቃ መሸጫ መተግበሪያ ሰርቶ ማስተዋወቁ ይታወሳል።

ኤልያስ በዘመናዊው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ አሻራቸውን ካሳረፉ ወጣት ባለሙያዎች መካከል አንዱ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎችና ለሙዚቃ ቅርብ የሆኑ ሰዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች የመሰከሩለት ከያኒ ነበር።

"ሙዚቃ ከነሙሉ ክብሯ በኤሊያስ በኩል ታልፋለች" ሲሉ የሚመሰክሩለት ባለሙያዎች፣ የድምፃዊ ቴዲ አፍሮን "አቦጊዳ" ፤ የሚካኤል በላይነህን በ"አንተ ጎዳና" የዘሪቱ ከበደን የሙዚቃ ሰንዱቆች ያቀናበረው ኤሊያስ መልካ ነው።

የሚኪያ በኃይሉን "ሸማመተው" የእዮብ መኮንንን "እንደ ቃል"፣ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ ኃይሌ ሩት፣ አረጋኽኝ ወራሽ፣ ኩኩ ሰብስቤን፣ ትዕግስት በቀለ፣ የትግርኛ ዘፋኝዋ ማህሌት ገብረ ጊዮርጊስ፣ ጌቴ አንለይ፣ ቼሊና የኤሊያስ ሥራዎች ካረፈባቸው ሥራዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

ኤሊያስ መልካ በተለያዩ ማሕበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሕብረ ዝማሬዎችን ያቀናበረ ሲሆን ከእነዚህም መካከል መላ መላ፣ ማለባበስ ይቅር፣ ለአፍሪካ ሕብረት፣ በትራፊክ አደጋ መከላከል ላይ ያተኮሩት ተጠቃሽ ናቸው።

ሁለገብ የሙዚቃ ባለሙያው ኤሊያስ መልካ ትዳር ያልመሰረተ ሲሆን፣ በተለያዩ ሥራዎቹ የተለያዩ ሽልማቶችንና እውቅናን ከተለያዩ ወገኖች አግኝቷል።

ኤልያስ መልካ እስከ ባለፈው ቅዳሜ ድረስ በፋና የድምፃውያን ተሰጥኦ ውድድር ላይ በዳኝነት ሲያገለግል መቆየቱን ለማወቅ ተችሏል።